Jonah 3

ዮናስ ወደ ነነዌ ሄደ

1 የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤

2“ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።”

3ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ። በዚህ ጊዜ ነነዌ ታላቅ ከተማ ነበረች፤ እርሷንም ከዳር እስከ ዳር ለመጐብኘት ሦስት ቀን ያስፈልግ ነበር። 4ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ። 5የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።

6ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ በደረሰ ጊዜ፣ ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሱንም አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ በዐመድ ላይ ተቀመጠ። 7ከዚያም እንዲህ ሲል በነነዌ ዐዋጅ አስነገረ፤

“ከንጉሡና ከመሳፍንቱ የወጣ ዐዋጅ፤

“ማንም ሰው ወይም እንስሳ፣ የከብት መንጋም ሆነ የበግ መንጋ፣ ምንም ነገር አይቅመስ፤ አይብላ፤ ውሃም አይጠጣ።
8ነገር ግን ሰውም እንስሳም ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ ሰዎችም ሁሉ ክፉ መንገዳቸውንና የግፍ ሥራቸውን ይተዉ። 9እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ራርቶ ከጽኑ ቍጣው ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”

10እግዚአብሔርም ምን እንዳደረጉና ከክፉ መንገዳቸውም እንዴት እንደ ተመለሱ ባየ ጊዜ ራራላቸው፤ በእነርሱም ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላደረገም።

Copyright information for AmhNASV